የእምነት አንቀጽ (Our Belife)

 
የቤተ ክርቲያናችን መሠረታዊ እምነት (Our Belife)

የቤተ ክርስቲያናችን መሠረታዊ የእምነት መግለጫ (በአጭሩ የቀረበ)
ቤተ ክርስቲያናችን (መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን መሠረት አድርጋ ዝርዝር ገለጻውም እንደተጠበቀ ሆኖ) ከዚህ የሚከተለው
መሠረታዊ የእምነት አቋም አላት፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ፡ በእግዚአብሔር መንፈስ ፍጹም ተቆጣጣሪነት በሰዎች የተጻፉት ስድሳ ስድስቱ (39ኙ የብሉይ ኪዳን
እና 27ቱ የዐዲስ ኪዳን) መጽሐፍት ምንም ስህተት የሌለበት፣ እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች የገለጠበት፣ ኢየሱስ
ክርስቶስን በማመን መዳን የሚገኝበትን መለኮታዊ ዕውቀት የሚሰጥ ሉዓላዊ ሥልጣን ያለው መንፈሳዊ መጽሐፍ እንደሆነ
ታምናለች፡፡
እግዚአብሔር፡ ያልተፈጠረ፣ ሁሉን የፈጠረ፣ ዘላለማዊ፣ ሁሉን የሚችል፣ ከሁሉ በላይ የሆነ፣ በምንም የማይመሰል፣
ሉዓላዊ አሃዱ ሥሉስ አምላክ – ያህዌ እንደሆነ ታምናለችም (ዘዳ 6፣4-5\ 1ኛ ጢሞ 6፣16)፡፡
እግዚአብሔር አብ፡ የሁሉ ነገር ምንጭ እና መሠረት እንደሆነ፣ ፍጥረትን በማስተዳደርና በመዋጀት፣
በመጨረሻው ፍርድ ያለውን ፍጹም ሥልጣንና ሉዓላዊነት ታምናለች (ሮሜ 9፣15-16)፡፡
እግዚአብሔር ወልድ፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ዘላለማዊና አንድያ ልጅ መሆኑን፣ በመንፈስ
ቅዱስ ተፀንሶ ከድንግል ማሪያም መወለዱን፣ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መሆኑን፣ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት
ሞቶ በሦስተኛው ቀን መነሳቱን፣ ማረጉን፣ በአባቱ ቀኝ መቀመጡን፣ የቤተ ክርስቲያን መሥራችና ራስ መሆኑን
እንዲሁም ዳግም ለፍርድ እንደሚመጣም ታምናለች (ሉቃ 1፣34-35)፡፡
እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡ ሙላተ አካል ያለው መለኮት መሆኑን፣ ዓለምን ስለ ኃጢአት፣ ስለ ጽድቅ እና ፍርድ
የሚወቅስ መሆኑን፣ በአማኞች ውስጥ አድሮ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራቸው፣ የሚያጽናናቸው፣
የሚያስተምራቸው፣ የቅድስና ኑሮ ለመኖር እንደሚያስችላቸው፣ ለአገልግሎትም ኃይል እንደሚሰጣቸው፣ ቤተ
ክርስቲያን እንድትታነጽ የጸጋ ስጦታዎችን ለአማኞች የሚስጥ መሆኑን ታምናለች፡፡
ቤተ ክርስቲያን፡ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመንና በአንድ መንፈስ በመጠመቅ ዳግም የተወለዱ አማኞችን ሁሉ
የምታቅፍ የመሲሑ ሙሽራ መሆኗን፣ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ መታነጿን፣ ራስና መሥራቿ ክርስቶስ መሆኑን
እርሷም አካሉ መሆኗን ታምናለች (ኤፌ 1፣22-23)፡፡
ፍርድ፡ ጌታ ኢየሱስ ዳግመኛ ወደ ምድር ሲመጣ በሰዎች ሁሉ ላይ እውነተኛ ፍርድ እንደሚያደርግ፣ ያመኑት ወደ
ተዘጋጀላቸው የዘላለም በረከትና እውነት ሲገቡ በእርሱ ያላመኑ ሰዎች ከሰይጣንና ርኩሳን መንፈሳውያን ኃይላት ጋር ወደ
ዘላለም ሞት እንደሚጣሉ ታምናለች (2ኛ ተሰ 1፣8-10\ ራዕ 21፣6-8)፡፡
ቅዱሳን መልዐክት፡ በእግዚአብሔር ፊት እርሱን የሚያመልኩና ፈቃዱን የሚያገለግሉ፣ በእርሱም የተፈጠሩና መናፍስት
መሆናቸውን እንዲሁም የእግዚአብሔርን ዐሳብ ለማገልገል በምድር ለሰዎች ሊገለጡ እንደሚችሉ ታምናለች (ሉቃ 1፣27\
ዕብ 1፣14)፡፡
ሰይጣን፡ በእግዚአብሔር ላይ ያመፀ ርኩስ መንፈስ መሆኑን እና በመጨረሻው ፍርድ ከተከታዮቹ ጋር ወደ እሳት ባሕር
እንደሚጣል ታምናለች (ማቴ 25፣41\ ራዕ 20፣10)፡፡
ሰው፡ በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩን፣ በኃጢአት መውደቁንና በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቁጣ\ ፍርድ ያለበት
በደለኛ መሆኑን፤ መንፈስ፣ ነፍስ እና ሥጋ ያለው ፍጡር መሆኑን ታምናለች (ዘፍ 1፣26-27፤ 2፣6-7\ 1ኛ ተሰ 5፣
23)፡፡
ውድቀት፡ ሰው ሲፈጠር ከኃጢአት ነጻ ሆኖ መፈጠሩን፣ በራሱ ስህተት በኃጢአት መውደቁን፣ ከእግዚአብሔር ተለይቶ
መጥፋቱን፣ መንፈሳዊ እና ስጋዊ ሞት መሞቱን፣ ከሰይጣን ሥልጣን በታች መዋሉን ከዚህ የተነሳም ፍጥረት ሁሉ ከርግማን
በታች መውደቁን ታምናለች (ዘፍ 3፣6)፡፡
ድነት፡ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ብቻ በነጻ የሚገኝ መሆኑን፣ ያመነ ሰው ከኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ ጋር ኀብረት ለማድረግ
መጠመቅ እንደሚኖርበት፣ የዳነ ሰው በመሲሑ ዳግም ምጽዓት የድነቱን ሙላት እንደሚቀበልና የትንሳኤ አካል እንደሚለብስ
ታምናለች (ሮሜ 10፣9\ ፊልጵ 3፣20-21\ 1ኛ ተሰ 4፣14-18)፡፡
የክርስቶስ ዳግም ምጽዓት፡ ክርስቶስ በእርሱ ያመኑትን ሁሉ ወደ ራሱ ለመሰብሰብ ዳግም እንደሚመጣ፣ የብሉይና ዐዲስ
ኪዳን አማኞች ሁሉ እርሱን ለመቀበል እንደሚነጠቁ እና ከእርሱ ጋር እንደሚኖሩ ታምናለች (1ኛ ቆሮ 15፣20-21\ 1ኛ
ተሰ 4፣14\ ራዕ 20፣11-15)፡፡

ማስታወሻ፡
የቤተ ክርስቲያናችንን መሠረታዊ የእምነት መግለጫ በዝርዝር ለማግኘት የድረ ገጹን አስተዳዳሪ ያግኙ፡፡

ስለ እኛ ተጨማሪ

Follow by Email
YouTube